በጥቂቱም ቢሆን ዕድሜ እየተጫጫናቸው መምጣቱ ከፊታቸውና ከመላ ሰውነታቸው ይነበባል፡፡ በተለይም ጣታቸው፣ እጃቸው፣ ክንዳቸውና ቀሪ ሰውነታቸው ጠንከርከር የሚለው መድረክ ላይ ወጥተው ማሲንቋቸውን ሲይዙ ነው፡፡
የ72 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ አራጌ ኢማሙ በወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ውስጥ ማሲንቆ ተጫዋች ሲሆኑ ከ23 ዓመታት በፊት የፈረሰው የቀድሞው ወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ውስጥም ሙዚቀኛ ነበሩ፡፡
አቶ አራጌ እንደሚናገሩት በ1960ዎቹ ‹‹የወሎ የሀገር ባህል ተጫዋቾች ክበብ›› በሚል የተመሠረተው ቡድን 97 አባላት ነበሩት፡፡ ‹‹መሬት ላራሹ›› ከታወጀ በኋላ የቡድኑ አባላት ወደ እርሻና ወደ ሌላም ሥራ ተሰማርተው ይበተኑና የአባላቱ ቁጥር ይቀንሳል፡፡ የቀሩት አባላት በቀለመወርቅ ደበበ ሥር ሆነው ወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን በሚል መንቀሳቀስ ይጀምራሉ፡፡
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን በተነሳ ቁጥር ከአፍ የማትነጠለው ማሪቱ ለገሠን ጨምሮ ዝነኛዋ ዚነት ሙሀባ፣ ወርቅነሽ ተጫን፣ ፀሐይ አበራ፣ ዙሪያሽ አብዩ፣ ፀሐይ ካሳ፣ መሀመድ ይመርና ትግስት አባተጫን የመሳሰሉ የቡድኑ አባላትን በርካቶች ዛሬ ድረስ ያስታውሳሉ፡፡ የቡድኑ የቀድሞም የአሁንም አባል አቶ አራጌ ከማሲንቆ በተጨማሪ አኮርዲዮን መጫወትና ማንጎራጎር የሚሞክሩ ሲሆን፣ የያኔው የኪነቱ አባላት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አንስተው ያገኙት የነበረውን አነስተኛ ገንዘብ ሲያስታውሱ ይገረማሉ፡፡
በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በወቅቱ ጥራቱን የጠበቀ ዜማ፣ ግጥሙ ያማረና ባህልን ጠንቅቆ የተከተለ ሥራ የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ይሠራ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በሐሳቡ የሚስማሙት አቶ አራጌ በተለይ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ‹‹ፈጣኑ ባቡሩ›› እና ሌሎች በርካታ ተወዳጅ ዜማዎች እንደነበሯቸው ይናገራሉ፡፡ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ‹‹ፈጣኑ ባቡሩን›› ተጫውተው በወቅቱ ከደርግ ሊቀመንበር ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መጓጓዣ መኪና ማግኘታቸውን ያወሳሉ፡፡
ወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ከተበታተነ በኋላ የአብዛኞቹ ዕጣ ፈንታ እንደሆነው ሁሉ ራሳቸውን ለማስተዳደርና ቤተሰብ ለመደጎም በተለያየ አገር እየተዘዋወሩ ማሲንቆ ይጫወቱ ነበር፡፡ ዛሬ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አራጌ ሙዚቃ በጀመሩበት ወቅት ሙያው ባይከበርም ለሙያው ያደረጉትን ጥረት ይናገራሉ፡፡
ከቡድኑ ወጥተው ከገጠማቸው ውስጥ ያጫወቱን፣ በአንድ ወቅት ባለቤታቸው የነበሩት ሴት ልጅ ወልደው ይሞትባቸዋል፡፡ ልጁ ሲሞት የባለቤታቸው ቤተሰቦች ‹‹የላሊበላ ልጅ ምን ያደርግልሻል›› እያሉ ያጥላሏቸው ነበር፤ በዚህ የተነሳ ለፍቺ እንደተዳረጉም ይናገራሉ፡፡
‹‹በሙያው ስንናቅበት ኖረናል›› የሚሉት ሙዚቀኛው ዛሬ ላይ የተሻለ አመለካከት አለ ብለው ስለሚያምኑ ዳግም የወሎ ላሊበላ ቡድን አባል መሆናቸውን በበጎ ያዩታል፡፡ አቶ አራጌ የያኔው ቡድን ላይ የሚደርስ የለም ቢሉም፣ ምንም ቢሆን ደግሞ መሰባሰቡና የሙዚቃ ሕይወትን በኅብረት መግፋቱ መልካም ነው ባይ ናቸው፡፡ በቡድኑ ዳግም ዕድል ያገኙት ባለሙያው ሕይወቴ እስካለ ድረስ በቡድኑ ውስጥ እኖራለሁ ይላሉ፡፡
ዛሬ ላይ ሆነው ወደ ኋላ ሃያ ሦስት ዓመታትን አሻግረው ሲመለከቱ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራ አሳርፎ፣ ተተኪን አፍርቶ ለመዝለቅ ይንደረደር የነበረው ታላቁ የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን መበተኑን በርካቶች በቁጭት ይናገራሉ፡፡
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን በደርግ ወቅት በተበረከተላቸው መኪና በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ በተሰጣቸው ኃላፊነት በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረዋል፡፡ አገራዊ መልዕክት ካሏቸው ሙዚቃዎች በተጨማሪ ልዩ ልዩ ቅኔያዊ ትርጓሜ ያላቸው ሥራዎች ካበረከቱት የቡድኑ አባላት አንዳንዶቹ ጥላሁን ገሠሠና መሀሙድ አሕመድን የመሰሉ ሙዚቀኞች የነበሩበት የሕዝብ ለሕዝብ ቡድን አባላትም ነበሩ፡፡
በርካታ ድምፃውያን፣ ተወዛዋዦችና የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ያፈራው ይህ ቡድን ኢሕአዴግ ሲገባ አባላቱ ተበታትነው ገሚሱ በሙዚቃ ሕይወታቸው ሲቀጥሉ ቀሪው ወደ ሌላ ሕይወት ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ የቡድኑ መፍረስ ዘወትር ይቆረቁራቸው የነበሩ አባላቱ በተለይም ቀድሞ በቡድኑ ከበሮ ተጫዋች የነበረው ዳምጤ መኰንን (ባቢ) ከረዥም ጊዜ ጥረት በኋላ በምሥራቅ አማራ ያሉ ወጣቶችን መልምለውና ከቀድሞ ቡድን ጥቂት አባላት አክለው ዳግም በኅብረት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ይህ የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን በአዲስ አወቃቀር ከተቋቋመ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የተመለመሉት ወጣቶች ለስድስት ወር ያህል በወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮምቦልቻ ካምፓስ ውስጥ ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ መስከረም 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ቡድኑ በይፋ ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ቡድኑ ደሴ ውስጥ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወረ ሙዚቃና ውዝዋዜ አጣምሮ ያቀርባል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ጥር ወር በተካሄደው 4ኛው የባህል ፌስቲቫል ላይ ክልሉን ወክሎም ቀርቦ ነበር፡፡
ከዓመታት በኋላ ዳግም የተነሳው ቡድኑ ድምፃውያን፣ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችና ተወዛዋዦችን አጣምሮ 34 አባላት የያዘ ሲሆን፣ በርከት ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ ከልዩ ልዩ ባህላዊ መገለጫዎች ጋር ያቀርባል፡፡
በአማራ ልማት ማኅበር በተገነባ ማዕከል መድረክ ላይ ያየናቸው የቡድኑ አባላት አንድ ብሔረሰብን ከሚገልጽ አልባሳት ወደ ሌላው ቀይረው በአዲስ ኃይል ወደ መድረኩ ለመመለስ የሚወስድባቸው ጊዜ አጭር ነው፡፡ ለአንድ ምሽት የሚያቀርቧቸውን ብሔረሰቦች ውዝዋዜ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን መገለጫ ባህል በአጫጭር ሙዚቃዊ ተውኔቶች ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡
ከወጣቶቹ አንዱ ሀብታሙ መሀመድ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ውዝዋዜ ወቅት ፊቱ ላይ ለተወዛዋዥነት ያለውን ፍቅር ማንበብ ይቻላል፡፡ ከአንድ እንቅስቃሴ ወደሌላ እንቅስቃሴ በተዘዋወረ ቁጥር ለሙያው ካለው ፍቅር አሻግሮ ችሎታውን መመልከት ይቻላል፡፡
ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሐይቅ የተወለደው ሀብታሙ የ22 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የመሰናዶ ትምህርቱን እየተከታተለ በነበረበት ወቅት የኪነት ቡድን አባል መሆን ለሚሹ የተደረገ መጥሪያ ይሰማል፡፡ ልጅ ሳለ አንስቶ ወደ ሙዚቃው ዓለም መቀላቀል ምኞቱ ነበረና ሳያመነታ ጥሪውን ተቀብሎ ተወዳደረ፡፡
ውድድሩን አልፎ በሥልጠናው ወቅት በየወሩ መገምገሚያ ፈተና የነበረ ሲሆን፣ ከመጀመሪያው አንስቶ የነበሩትን ዙሮች አልፎ የመጨረሻው ዙር ውስጥ የቡድኑ አባል ከሆኑት ተወዛዋዦች መካከል ተቀላቅሏል፡፡ ሀብታሙ ባህላዊ ውዝዋዜ ሲያቀርብ ሐሴት ቢሰማውም ‹‹የተፈጠርኩበት ወሎን ያህል የምወደው ጭፈራ የለም፤›› ይላል፡፡
ሀብታሙ ዛሬ የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ዳግም መቆርቆር ምክንያት በየዕለቱ በሚወደው ሙያው ውስጥ እንደሚኖር በሀሴት ተሞልቶ ይናገራል፡፡ የታሪካዊው ባህላዊ ቡድን አባል ከመሆን ባሻገር በሙያው የረዥም ዓመታት ዝናን ካተረፉ ባለሙያዎች ጎን መሥራቱና በየዕለቱ የውዝዋዜ ችሎታውን ለማሳደግ ዕድል ማግኘቱ ያስደስተዋል፡፡ የቡድን አጋሮቹ እርስ በርስ ልምድ ከመለዋወጥና ከመተራረም በዘለለ በፍቅር የሚሠሩ መሆኑ ሙያዊ ሕይወቱን ቀና እንዳደረገለትም ይናገራል፡፡
ወጣቱ ወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን በአካባቢው ባሉ ሰዎች የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ከማስተዋወቁም በላይ የቀድሞውን ባህላዊ ቡድን ሕይወት የዘራበትና ደሴን በማስተዋወቅ ረገድ በበጎ እንደሚያነሳቸውም ይናገራል፡፡
ከአንድ ድምፃዊ ጓደኛው ጋር የሚኖረው ሀብታሙ የባህል ቡድኑ በተለያዩ ቦታዎች የሚደረግለት ጥሪ ያስደስተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ጎንደርና ሌሎች አገሮች በመሄድ ያቀረቡትን ዝግጅት በትውስታ የሚያወሳው ሀብታሙ በውዝዋዜ ዝነኛ የሆኑትን እያጣቀሰ ነገ እነሱ የደረሱበት የመድረስ ህልሙን አስረግጦ ይናገራል፡፡
ሌላው ወጣት ሀዲሴ ገብረማርያም በአዲስ አበባ እምብርት አራት ኪሎ የተወለደ ሲሆን፣ ቡድኑን በባህል ውዝዋዜ ሥልጠና ለማገዝ በሚል ከዓመት በፊት ወደ ደሴ ያቀናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ የባህል ቤቶች ተወዛዋዥ የነበረው ሀዲሴ የወሎ ላሊበላ ቡድን አባላትን ከተመለከተ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባን ተሰናብቶ ደሴ ላይ ከትሟል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ብትናፍቀኝም፤ የወሎ ላሊበላ ባህል ቡድን ፍቅራቸው አሸንፎኛል፤›› የሚለው ሀዲሴ ቡድኑ እንቅስቃሴ የጀመረ ሰሞን አዲስ አበባ መጥተው ለምክር ቤት ያቀረቡትን ዝግጅት ያስታውሳል፡፡
በባህል ማዕከሉ ውስጥ የሚስረቀረቅ ዜማ ካቀረቡት አንዷ ዓለም ውቤ በወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ውስጥ ድምፃዊት ናት፡፡ በተወለደችበት አካባቢ የነበረ የገበሬ ማኅበር ኪነት አባል ከመሆን ተነስታ የዚነት ሙሀባን ዘፈኖች ዳግም ተጫውታ አልበም አውጥታለች፡፡ ልጅ እያለች ‹‹መቅደላ›› በተሰኘ የኪነት ቡድን በነበረችበት ወቅት ከወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ጋር ሙዚቃ እየተዋዋሱ ይጫወቱ ነበር፡፡
የቀድሞ ወሎ ላሊበላ ቡድን ከፈረሰ በኋላ እሷም ከነበረችበት ቡድን የወጣችው ዓለም፣ ቡድኑ ዳግም በመነሳቱ ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች፡፡ በተለይም የወሎን ባህል ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ፍላጎት ያላት ዓለም ከቀደሙት ድምፃውያን የማሪቱ ለገሰንና የዚነት ሙሀባን ፈለግ ተከትሎ አልበሞች የማሳተም ህልም አላት፡፡
‹‹ሙዚቃ በመዋዋስ የማውቀው ቡድን ዛሬ ጠቅልዬ ገብቻለሁ በምንም የምላቀቅ አይመስለኝም፤›› የምትለው ዓለም፣ በወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን የቀድሞው ፍቅርና መተሳሰብን ዛሬ ማግኝቷ ዋጋ የማይከፈልበት መሆኑን ትናገራለች፡፡
ስለ ባህል ቡድኑ አስተያየታቸውን ከሰጡን ሌላው በኮካ ኮላ ሱፐር ስታርስ ውድድር ላይ ያለፈውን ዙር በአሸናፊነት ያጠናቀቀው ታደሰ መኰንን ነው፡፡ በደርግ ወቅት በነበረው ወታደራዊ ክፍል ሙዚቃዊ እንቅስቃሴውን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ፣ በመቀጠልም ወደ ደሴ ተመልሶ ኑሮውንና የሙዚቃ ሕይወቱን በትውልድ አገሩ አድርጓል፡፡
በቡድኑ በሙዚቀኝነት እንዲሁም በድምፅ በማሠልጠን የሚገኘው ታደሰ እሱ ብቻ ሳይሆን በርካቶች ቡድኑ ከፈረሰ በኋላ ያስቆጫቸው ነበርና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ አቅም የነበረው ባህላዊ ቡድን ለመመለስ ከሙያዊ አጋሮቹ ጋር ጥናት አካሂዷል፡፡
ታደሰ የባህል ቡድኑ ዳግም መቋቋሙ ተቀዛቅዞ የነበረውን የሙዚቃ መንፈስ የሚያነቃቃ፣ ቱባ ባህል የሚያስተዋውቅ፣ ለአገሪቱ የሚሆኑ ሙዚቀኞችን የሚያፈራ፣ ኅብረተሰቡን የሚያነቃቃ፣ የቱሪዝም ዕድገቱን የሚያነሳሳ ነው ይላል፡፡
ከምሥራቅ አማራ የተወጣጡ ቢሆንም መላው ኢትዮጵያን የሚወክል ቡድን እንደሆነ የሚናገረው ታደሰ፣ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ አልፎ በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ባህል አስተዋዋቂ እንደሚሆኑ ያለውን እምነት ይናገራል፡፡ በዕድሜ የገፉት ለተተኪ የሚሆን ዕውቀት እያስተላለፉ እንዲሁም ወጣት አባላቶች በጥቅም ሳይደለሉ በጥንካሬ የሚንቀሳቀሱበት እንጂ እንደቀድሞው በድንገት ያለምትክ የሚፈርስ እንደማይሆን ያለውን ተስፋም ይናገራል፡፡
የቡድኑን አባላት የመለመለው፣ የቡድኑ አሠልጣኝ እንዲሁም የቀድሞው ወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን አባል ዳምጤ እንደሚገልጸው ከደብረብርሃን እስከ ሰቆጣ ባለው አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች የቀድሞን የኪነት ቡድን ታሳቢ በማድረግ ተሰባስበዋል፡፡