Daniel Kibret እኛ፣ የመጨረሻዎቹ ፤ በዳንኤል ክብረት
በፌስ ቡክ የተለቀቀ አንድ ጽሑፍ በምዕራቡ ዓለም የ1950ዎቹን፣60ዎቹን፣ 70ዎቹንና 80ዎቹን ትውልዶች በተመለከተ ‹‹እኛኮ በቶምና ጄሪ ፊልም ያደግን፣ በመንገድ ላይ የተጫወትን፣ በሬድዮ ካሴት ሙዚቃ ያዳመጥን የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ነን፡፡›› ይላል፡፡
እኔም ይህንን ሳይ የራሴ ትውልድ ትዝ አለኝ፡፡
እውነትም እኮ እኛ የ1940ዎቹ፣ 50ዎቹና 60 ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ጠቅላይ ግዛት የሚባል አከላለል ክፍለ ሀገርም የሚባል አካባቢ፣ አውራጃ የሚባል ቦታ፣ ምክትል ወረዳ የምትባል ጎጥ ያየን፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ በምድር ላይ ሲጓዝ የተመለከትን፣ የንጉሥ ግብር የበላን ወይም ሲበሉ ያየን፣ ንጉሥ ሲወርድ፣ መሪም ሲኮበልል ለመታዘብ የቻልን፣ ደጃዝማችነት፣ ቀኝ አዝማችነት፣ ራስነት፣ ባላምባራስነት፣ ፊታውራሪነት፣ ነጋድራስነት፣ ጸሐፌ ትእዛዝነት፣ አጋፋሪነት፣ እልፍኝ አስከልካይነት ዓይናችን እያየ ታሪክ ብቻ ሆነው ሲቀሩ ምስክር የሆንን የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ነን እኛ፡፡
የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ጋዜጣ፣ መነንና መስከረም መጽሔት ገዝተን ያነበብን፣ የምሥራች ድምጽን ያዳመጥን፤ ሐዲስ ዓለማየሁንና ከበደ ሚካኤልን ጳውሎስ ኞኞንና ዳኛቸው ወርቁን፣ በዓሉ ግርማንና አቤ ጎበኛን በዓይናችን ያየን፣ አበበ ቢቂላ ሲሮጥ፣ ማሞ ወልዴ ሲያሸንፍ፣ ምሩጽ ይፍጠር በሞስኮ ኦሎምፒክ አረንጓዴው ጎርፍን እየመራ ሲፈተለክ፣ መንግሥቱ ወርቁ ሲጠበብ፣ ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካን እግር ኳስ ሲመራ፣ፍቅሩ ኪዳኔ እግር ኳስን ሊያስተላልፍ ሲታትር፣ ደምሴ ዳምጤ ‹ዳኙ ዳኙ ገልግለን› ሲል ያየንና የሰማን የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ነን፡፡
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
በ15 ሳንቲም አውቶብስ፣ በ35 ሳንቲም ታክሲ የሄድን፣ በውይይት ታክሲ የተሳፈርን፣ ከቀበሌ በቤተ ሰብ ልክ ስኳርና ዘይት የገዛን፣ በ50 ሳንቲም የቀበሌ ቤት ኪራይ የኖርን፣ የ10 ሳንቲም ዳቦ በአምስት ሳንቲም ሻሂ የጠጣን፣ ያምስት ሳንቲም ጮርናቄ የገመጥን፣ የመቶ ብሮች ጤፍ፣ የአሥር ብሮች ዶሮ የበላን፤ የሃያ ብር ቤት የተከራየን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
ጎረቤት ሄደን ቴሌቭዥን ያየን፣ ቴሌቭዥን ለማየት ብለን ለሀብታም ጎረቤት ያገለገልን፣ በነጭና ጥቁር ቴሌቭዥን የተዝናናን፣ በአባባ ተስፋዬ ተረት ያደግን፣ በወጋዬሁ ንጋቱ ትረካ ጥርሳችን የነቀልን፣ ‹‹ሾላ እርግፍ እርግፍ›› የተጫወትን፣ በ‹‹ማዘር ኢንዲያ›› ያለቀስን፣ ንፋስ እንደመታው የገብስ እህል እየተወዘወዝን ‹ሀ ግእዝ፣ ሁ ካእብ ሂ ሳልስ›› ብለን በልጅነት ያዜምን፣ ለትምህርት ቤት መመዝገቢያ ሃምሳ ሳንቲም፣ ለስፖርት አንድ ብር የከፈልን፤ በጆንትራ ቮልታ ያጌጥን፣ ሎሚ ተራ ተራ ዘፍነን ቡጊቡጊ የጨፈርን፤
እኛ የመጨሻዎቹ፤
በቪሲአር ካሴት ፊልም ያየን፣ በፎቶ ብቻ ያለ ቪዲዮ ሠርግ የሠረግን፣ ወይም ሲሠረግ ያየን፣ ፎቶ ተነሥተን በአሥር ቀን የደረሰልን፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችን ጋር ተደርድረንና ተቃቅፈን በነጭና ጥቁር ፎቶ የተነሣን፣ ያለ ሙዓለ ሕፃናት አንደኛ ክፍል፣ ያለ ‹ፕሪፓራቶሪ›› ኮሌጅ የገባን፣ ‹‹በየኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆርበት፣ በኛ ጎሮሮ አጥንት ይሰካበት›› ብለን ለመምህራችን ያዜምን፤ ትምህርት ቤት ለመግባት በቀኝ እጃችን በአናታችን በኩል ጆሯችንን እንድንነካ የተደረግን፣
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
ለዕድገት በኅብረት እንዝመት
ወንድና ሴት ሳንል በአንድነት
እየተባለ ዕድገት በኅብረት ሲዘመት ያየንና የተሳተፍን፣ ለሶማልያ ጦርነት ሲዘመት የነበርን፣ ለእናት ሀገር ጥሪ ቆሎ የቆላን፣ እንጀራ የጋገርን፤ ሲጋገርም ያየን፤ የ66ቱንና የ83ቱን አብዮት ያየን፤ መሬት ላራሹ ሲታወጅ፣ ትርፍ ቤት ሲወረስ፣ ‹የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት› በሬዲዮ ሲዘፈን ልባችን የቆመ፤ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር ሲፋፋም በመካከሉ ያለፍን፤ መኢሶን፣ ኢዲዩ፣ ኢጭአት፣ ኢማሌድህ፣ እየተባለ ሲፎከር ብናውቀውም ባናውቀውም የፎከርን፤ ከጫካ ይተላለፍ የነበረውን የኢሕአዴግ ሬዲዮ ተደብቀን ያዳመጥን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
የይለፍ ወረቀት ከቀበሌ አውጥተን ክፍለ ሀገርን ያቋረጥን፣ በኬላ ላይ ቆመን መታወቂያ አሳይተን ያለፍን፣ አኢወማ ገብተን፣ መኢሰማን አልፈን፣ አኢሴማ ተሳትፈን፣ በመኢገማ ተደራጅተን የፎከርን፣ የተሰለፍን፤ በዘመቻ ተወልደን በዘመቻ ያደግን፤ የውይይት ክበብ፣ የማሌ ጥናት የተሳተፍን፣ የሞስኮ ሬዲዮ ያዳመጥን፣ ወዛደራዊ ዓለማቀፋዊነትን ያነገብን፣ መደብን ከመተኛነት ወደ መደብ ትግል ያሸጋገርን፤ አድኃሪ፣ አቆርቋዥ፣ መሐል ሠፋሪ፣ ጨቋኝ፣ ተጨቋኝ፣ ቡርዡዋ፣ ከበርቴ፣ የአድኅሮት ኃይላት በሚባሉ ቃላት ዐርፍተ ነገር ሠርተን የተማርን፤
የኮምፒውተር መልኩን ብቻ ሳይሆን ስሙንም ሳንሰማ ኮሌጅ የደረስን፤ በዱላው ሞባይል ያናገርን፤ ከጎኑ እንደ ጉድጓድ ውኃ መዘወርያ እየተዘወረ በሚደወልበት ስልክ የደወልን፤ ከአናቱ አሥር ጊዜ ቀዳዳው ተይዞ እየተሸ ከረከረ በሚደወልበት ስልክ ሃሎ ያልን፤ ገንዘብ ስናጣ በተዘዋዋሪ የደወልን፡፡ የቤታችን ቴሌቭዥንና ስልክ ብርቅ ሆኖ በአበባ ተንቆጥቁጦ የተጠለፈ ልብስ ሲለብስ ያየን፤ ያለ ሞባይል፣ ያለ አይፎን፣ ያለ አይ ፖድ ያደግን፤ ያለ ዓረብ ሳትና ያለ ናይል ሳት፣ ያለ ኤፍ ኤምና ያለ ፍላት ቴሌቭዥን የኖርን፣ በታይፕ ራይተር የጻፍን፣ በታይፕ ራይተር የተፈተን፣ ያለ ዲኤስ ቲቪ እግር ኳስን በዜና ብቻ የተከታተልን፤ ከነ ማንቸስተር በፊት እነ ሊቨርፑልን የደገፍን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
እርሳሳችንን በምላጭ የቀረጽን፣ የአሥራ አራቱ ክፍላተ ሀገራት ካርታ ባለበት ደብተር የጻፍን፣ በአምስት ሳንቲም ሁለት በሚሸጥ ሉክ የተፈተንን፤ በጨርቅ ቦርሳ ደብተራችንን የያዝን፣ ምሳ ሳንይዝ ትምህርት ቤት የሄድን፣ በሁለትና በሦስት ፈረቃ የተማርን፤ የነ ጫልቱን ቤት፣ ለማ በገበያን፣ ሽልንጌን አንበን፣ በውሸታሙ እረኛ ተገሥጸን፣ የያደግን፤ እነ ማኦ ሴቱንግን፣ እነ ኪም ኤልሱንግን፣ እነ ማርሻል ቲቶን፣ ያደነቅን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
ውጭ ሀገር ለመሄድ ለኢሚግሬሽን ገንዘብ ያስያዝን፤ የመውጫ ቪዛ ያስመታን፣ በትንሷ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ውጭ የተጓዝን፣ የቦሌ ሠገነት ላይ ወጥተን ወዳጆቻችንን የሸኘን፣ ጣልያን በሠራው ድልድይ ዓባይን ያቋረጥን፣ ሮንድ ሲታደርና ስናድር ያየን፣ በሰዓት እላፊ ተይዘን የታሠርን፣ ሕዝብ ሃምሳ ሚሊዮን ሲሆን ምን እንደሚመስል የታዘብን፣ ከኮንዶም በፊት ተወልደን አሥር ሆነን ያደግን፤ ኢምፔሪያሊስቶች ባዘጋጁት ኦሎምፒክ አንሳተፍም ብለን የቀረን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
በአድዋ ጦርነት የነበሩ ሰዎች ሲናገሩ ያየንና የሰማን፣ በሦስት መንግሥት ብሮች የተገበያየን፤ በአለባቸውና በልመንህ ቀልዶች የተዝናናን፣ ኮንደሚንየም የሚባል ቤት ሳናውቅ በቁጠባ ቤት ያደግን፣ ‹ሪል እስቴት› የሚባል ስም ስናረጅ የሰማን፣ በማኅበር ተደራጅተን የቤት መሬት በነጻ ያገኘን፣ በሪል ካሴት ዜማ ያዳመጥን፣ በሬዲዮ ካሴት ብቻ የተቀረጹ ነገሮችን የሰማን፣ የቤት ውስጥ ማድ ቤት(ኪችን) ሳናይ ያደግን፣ በከተማ ወንዞች የዋኘን፣ ኢንተርኔት ሳናይ ብሎግ ሳናነብ፣ ዌብ ሳይት ሳናገላብጥ፣ ‹ሚሴጅ ቴክስት› ሳናደርግ፣ ያደግን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
በማይነከር ሻይ ቅጠል የጠጣን፣ ከኤይድስ በፊትም ከኤይድስ በኋላም የኖርን፣ የጣት እንጅ የመንገድ ቀለበት ሳናይ ያደግን፣ የሚፈስ እንጅ የሚታሸግ ውኃ ሳንጠጣ ለወግ ለማዕረግ የደረስን፣ በፌስቡክ ሳንወጣ፣ በትዊተር ሳንጽፍ ነፍስ ያወቅን፤
እኛ የመጨረሻዎቹ፤
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሕይወታችንን መዳረሻ የወሰነልን/ብን፣ 12ኛ ክፍል ተፈትነን መሠረተ ትምህርት የዘመትን፣ ታፍሰን ብሔራዊ ውትድርና የተላክን፣ ከኮሌጅ ወጥተን በመንግሥት ምደባ ሥራ የተቀጠርን፣ ሳንከፍል በመንግሥት ገንዘብ ኮሌጅ የበጠስን፣ አራት ኪሎንና ልደታን በጥንት መልኳ ያየን፣ በአንድ የክፍለ ሀገር አውቶብስ ተራ ሁሉንም ክፍለ ሀገር የተሣፈርን፣
እና የመጨረሻዎቹ፤
እንዲሁ ካሰብነው ስንቱ ነገር አልፎ ስንቱ ነገር መጥቷል፡፡ ለስንቱ ነገርስ እኛ የመጨረሻዎቹ ሆነናል፡፡ የትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በሃምሳ ሳንቲም ዶሮ፣ በሁለት ብር በግ፣ በዐሥር ብር በሬ፣ በአምስት ብር ኩንታል ጤፍ ገዛን ሲሉን እንደተረት እንሰማው ነበር፡፡ ዛሬ እኛም ተረት ልንሆን ነው፡፡ አሁን ዶላር በሁለት ብር መነዘርን፣ ስኳር በአንድ ብር ገዛን፣ ጤፍ በአርባ ብር ሸመትን፣ ቤት በዐሥር ሺ ብር ሠራን፣ ብንል ማን ያምነናል? እኛ ራሳችን ተረት ልንሆንኮ ትንሽ ነው የቀረን፡፡
እስኪ እናንተም የመጨረሻ የሆናችሁበትን አስታውሱት፤ እኔ የረሳሁትን ብዙ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ ለካስ ታሪክና ተረት እንዲህ እየሆነ ነው የሚፈጠረው፡፡ ‹ነበር ለካስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል›› አሉ እቴጌ ጣይቱ፡፡