አገር አቀፍ የአሠልጣኞችና ዳኞች ማኅበር ተመሠረተ
በአገሪቱ ቀደምት የምሥረታ ታሪክ ካላቸው ስፖርቶች አትሌቲክስ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ስፖርቱ ምንም እንኳ በሥሩ የሚያቅፋቸው የተለያዩ የሜዳ ተግባራት ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑ እንደተጠበቀ፣ በሩጫው ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪነቱ አገሪቱን በመድረኩ ከታላላቆቹ አገሮች ተርታ እንድትመደብ ያስቻለ መሆኑ አያከራክርም፡፡
ለሩጫው ስፖርት እዚህ መድረስ የዘርፉ አካል ተደርገው ከሚወሰዱት የአሠልጣኞችና ዳኞች ሚና ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ወሳኝ የሙያው አካላት እስከምንገኝበት ዘመን ድረስ የሙያተኛውን መብትና ግዴታ ሊያስጠብቅ የሚችል ምንም ዓይነት የሙያ ማኅበር ሳይኖራቸው መቆየቱ ተቋሙን ከሚያስወቅሱት ክፍተቶች በዋናነት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡
ይህንኑ የተረዳ የሚመስለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሐሙስ በኢትዮጵያ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባዘጋጀው መድረክ፣ አገር አቀፍ የአሠልጣኞችና ዳኞች ማኅበር የሚቋቋምበትን ረቂቅ ደንብ ለውይይት አቅርቧል፡፡ ረቂቅ ደንቡ ላይ የክልል ፌዴሬሽኖች አመራሮች፣ አሠልጣኞችና ዳኞች እንዲወያዩበት ሐሳብ እንዲሰጡበት ካስደረገ በኋላ የአሠልጣኞችና የዳኞች ማኅበር በይፋ በመመሥረት የአመራሮች ምርጫም አከናውኗል፡፡
ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ በክልል ደረጃ የአዲስ አበባ አስተዳደር 89 አባላት የሚገኙበት የዳኞችና 51 አባላት የሚገኙበት የአሠልጣኞች ማኅበር፣ በትግራይ ክልል 51 አባላት ያሉት የዳኞችና 41 አባላት ያሉት የአሠልጣኞች ማኅበር ተቋቁመው ክልላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይቷል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ክልል 30 አባላት ያሉት የዳኞችና 23 አባላት ያሉት የአሠልጣኞች፣ በኦሮሚያ 65 አባላት ያሉት የዳኞችና 47 አባላት ያሉት የአሠልጣኞች፣ በአማራ 20 አባላት ያሉት የዳኞችና 27 አባላት ያሉት የአሠልጣኞች፣ እንዲሁም በሐረር ክልል 15 አባላት ያሉት የዳኞችና 20 አባላት ያሉት የአሠልጣኞች ማኅበር ተቋቁመው በድምሩ 270 ዳኞችና 209 አሠልጣኞች በክልል ደረጃ በማኅበር ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ከቀሩት ውስጥ የድሬዳዋ አስተዳደርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳኞችና አሠልጣኞች ማኅበር ለመመሥረት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ አፋር፣ ኢትዮጵያ ሱማሌና ጋምቤላ ክልሎች ግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ አለመሆኑ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡